Ethiopia: በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ማንንም አታታልሉም!

People smiling
ከሕዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ላይ እጃችሁን አንሡ!
—————————
የሕዝበ ሙስሊሙን ስም ባገኙት አጋጣሚ ለማጥፋት የሚፈልጉ አካላት በሕዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ላይ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ መንዛት ጀምረዋል። የዛሬው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሰለባ ደግሞ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እና የታሪክ ምሑሩ Ahmedin Jebel ሆኗል። አሕመዲንን አገር የማፍረስ ተልእኮ እንዳለው እና የኦነግ አባልም እንደሆነ አድርገው ከዐውድ ውጭ የወጡ ፎቶዎችን እያስደገፉ ማሳየታቸውን ቀጥለዋል። እውነታውን ለሕዝብ ማሳወቅ ጠቃሚ ስለሆነ አሕመዲን ጀበልንም ሆነ የለጠፏቸው ፎቶዎች ላይ ያለውን የ Raadiyoo Daandii Haqaa – RDH ጋዜጠኛ እና አክቲቪስት Hayder Abdiiን ደውዬ አነጋግሬያቸው ነበር። በሰበሰብኩት መረጃ መሠረት እውነታውን ከውንጀላዎቹ ጋር እያመጣን አንድ ላይ እንፈትሻቸው እስቲ፦
.
———
ውንጀላ 1፦
———
.
አሕመዲን ጀበል ከራዲዮ ዳንዲ ሐቃ ሪፖርተር እና አክቲቪስት ሐይደር አብዲ ጋር በአሕመዲን ጀበል መኪና ውስጥ እና በሌሎችም ልጁ ሊዘግብ በተገኘባቸው አጋጣሚዎች የተነሡትን ፎቶዎች በማሳየት አሕመዲን ኦነግ ስለመሆኑ ጽፈዋል። ይህ አስቂኝ ክስ ነው። ጋዜጠኛ እና አክቲቪስት ሐይደር አብዲ በየቦታው እየተገኘ መዘገብ ሥራው ነው። አሕመዲን ጀበል በተገኘባቸው ፕሮግራሞች ላይም በተደጋጋሚ ተገኝቷል። ለምሣሌ አሕመዲን ዘመናዊ መኪና በተሸለመበት ወቅትም ሆነ በአገረ ኬንያ ለዓመታት ተሰድዶ ለቆየው ሙንሺድ አነስ ሙሐመድ ከሣምንታት በፊት አቀባበል በተደረገለት ወቅት ፎቶ ተነሥተዋል። ከውንጀላው ጋር ሼር ባደረጉት ሌላ ፎቶ ደግሞ አሕመዲን ጀበል ከእስር ሲፈታ ሐይደር ሄዶ ዘይሮት አብሮ ቆሞ ይታያል። በወቅቱ አሕመዲን በሺዎች በሚቆጠሩ ሙስሊሞች ይዘየር እና ፎቶ ይነሣ ነበር።
.
ሐይደር የተነሣቸውን ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ሼር የማድረግ ልምድ እንዳለው ለማወቅ አካውንቱን ከላይ ባለው ሊንክ ከፍቶ ማየት ብቻ ይበቃል። በገጹ ውስጥም ሆነ ከታች ባያያዝኳቸው ፎቶዎች ጋዜጠኛ ሐይደር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አባት ጋር፣ ከተፈናቃዮች ጋር፣ ከታማሚዎች ጋር፣ ከኡስታዝ አቡበክር ጋር፣ ከፖሊሶች ጋር፣ ከወታደሮች ጋር፣ ከሕፃናት ጋር ወዘተ ፎቶ ሲነሣ ይታያል። ጋዜጠኛ እና አክቲቪስት እንደመሆኑ ደግሞ ይህን ማድረጉ የሚጠበቅ ነው። አስገራሚም አይደለም።
.
ራዲዮ ዳንዲ ሐቃ የኦሮሚያ ትግሎች ላይ አትኩሮ የሚዘግብ ሚዲያ እንደመሆኑ መጠን ጋዜጠኛ ሐይደርም የቄሮ ትዕይንተ ሕዝቦች እና የተለያዩ ሕዝባዊ ፕሮግራሞች ላይ እየተገኘ ይዘግባል። የሙስሊሙን ወኪሎች ለማንቋሸሽ አጋጣሚ የሚጠብቁት የሐሰት ወንጃዮች ታዲያ በእነዚሁ ሠልፎች ላይ የተነሣውን አንድ ፎቶ በመውሰድ እና ከአሕመዲን ጋር የተነሣውን ሌላ ፎቶ አብረው በማምጣት የሐሰት ውንጀላቸውን ሠንዝረዋል። ነገሩ እንዲህ ነው፦
.
በኦቦ ዳውድ ኢብሳ አቀባበል ቅድመ ዝግጅት ወቅት በአዲስ አበባ ባንዲራዎችን እና የትግል ዓርማዎችን ለመስቀል በሚደረገው ጥረት ወቅት ግጭት እንዳይፈጠር ከተቋቋመው የሠላም ግብረ ኃይል መካከል ጋዜጠኛ ሐይደርም ከአየር ጤና አብሮ ተመድቦ ነበር። ሐይደር ግብረ ኃይሉ ውስጥ የገባው በሕዝብ ጥቆማ መሆኑን እና ከፖሊሶች ጋር አብሮ ሲሠራ መዋሉን ነግሮኛል። ፎቶውን የተነሣውም ዓርብ ከሰዓት 9 ሰዓት አካባቢ የቢሊሱማ ዓርማ ያለውን የደንብ አስከባሪ ልብስ እንደለበሰ መሆኑን የገለጸልኝ ሲሆን አስፈላጊ ከሆነ ከቀበሌው ደብዳቤ ማቅረብ የሚችል መሆኑን አብራርቶልኛል። ገጹ ውስጥ ከፖሊስ እና አድማ በታኝ ወታደሮች ጋር ሳይቀር ፎቶ ተነሥቶ የለጠፈውን ማየት ይቻላል። ሐይደር በፌስቡክ በይፋ የለቀቃቸው ፎቶዎቹ በነውረኛ አሉባልተኞች እጅ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በመዋላቸው እንደከፋውም አልደበቀኝም። ይህ ዓይነቱ ርካሽ ተንኮል ግን የአሉባልተኞቹን ጭምብል ከመግለጥ ውጭ ትንሽ እንኳ ማገናዘብ ለሚችል አዕምሮ የሚዋጥ አለመሆኑ ግልጽ ነው።
.
አሕመዲን ጀበል የሕዝብ ጀግና ነው። ለሕዝበ ሙስሊሙ የመብት ትግል አምባገነኑን መንግሥት ተጋፍጦ ከፍተኛ መስዋእትነት የከፈለ፣ ለከፍተኛ ሥቃይ እና ለዓመታት እስር ያልተበገረ የሕዝበ ሙስሊሙ ኮሚቴ አባል ነው። የለውጡ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለአዲስ አበባ የመገናኛ ብዙኀን የቦርድ አባልነት እና ለሕዝበ ሙስሊሙ ተቋማዊ አንድነት ጊዜያዊ ኮሚቴ አባልነት የመረጠው እምነት የሚጣልበት የአገር ጀግና ነው። በየሄደበት የሚያውቁት ሰዎች አብረውት ፎቶ ይነሣሉ። ይህ ሁሉም ታዋቂ ሰዎች ዘንድ የተለመደ ነገር ነው። እኒህን ለሕዝብ የተለቀቁ ኖርማል ፎቶዎች ልክ በከፍተኛ የምርምር ሥራ የተገኙ አስመስለው እና የሐሰት አጀንዳ ቀጣጥለው ሰው ያምነናል ብለው ፕሮፓጋንዳ መንዛታቸው እጅጉን ያስተዛዝባል።
.
———
ውንጀላ 2፦
———
.
ሁለተኛው ውንጀላቸው ደግሞ የታሪክ ምሑሩ አሕመዲን ጀበል፣ ጃዋር ሙሐመድ፣ ኦቦ በቀለ ገርባ፣ ኡስታዝ አቡበክር አሕመድ፣ ኡስታዝ አሕመድ ሙስጠፋ፣ ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ገቢሳ እና ሌሎችም በተገኙበት ገንፎ ሲበሉ የተነሣ ፎቶ በማሳየት እንዲሁ ተመሳሳይ የአገር አፍራሽነት እና የኦነግ አባልነት ድምዳሜ ሰጥተዋል። ይህም አስቂኝ ውንጀላ ነው። ስለፎቶው መጀመሪያ እናውራ እና መደምደሚያው ሁለት ሜትር እንኳ የማያራምድ ከሸረሪት ድር የደከመ ሎጂክ መሆኑን አብረን እናያለን።
.
ፎቶው የተነሣው ባለፈው ቅዳሜ የኦነጉ መሪ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ በመጡበት ቀን ነው። ፎቶው ላይ የሚታዩት የኮሚቴው አባላት በአቀባበል ሥርዓቱ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ያልተደረገላቸው ቢሆንም በአርበኞች ግንቦት 7 የካፒታል ሆቴል ዝግጅት ላይ የተገኙ በመሆኑ ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ላለማሳየት በሚል ወደኦቦ ዳውድ አቀባበል ለመሄድ ያስባሉ። ቀኑ ሳይታሰብ ስለደረሰ ቅዳሜ ጠዋት ጀዋር ጋር ደውለው ጥሪ እንዳልደረሳቸው፣ ግን መገኘት እንዳሰቡ ሲነግሩት «አሁን ቤት ከመጣችሁ አብረን መሄድ እንችላለን» ይላቸዋል። መኖሪያ ቤቱ ሲደርሱ አጋጣሚ ቁርስ ቀርቦ ስለነበር አብረው በሉ። ፎቶዎችንም ተነሡ። አሕመዲን ለብቻ ከጃዋር ጋር የተነሣውን ፎቶ ራሱ ኡስታዝ አቡበክር ነበር ያነሣቸው። ከኡስታዝ አቡበክር ጋርም እንደዚያው። ኤርፖርት ላይም ተመሣሣይ ፎቶዎችን ተነሥተዋል። እንግዲህ እኒህን በየቦታው እና በይፋ የተለቀቁ ኖርማል ፎቶዎችን እየሰበሰቡ ነው አሕመዲንን በኦነግነት እየወነጀሉ ያሉት። አሁን ደግሞ የሎጂኩን አይረቤነት እንየው።
.
የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው አባላት አገራዊ ጀግኖች ናቸው። ታዋቂዎች ናቸው። በየፕሮግራሙ ላይ ይጠራሉ። ከኦሮሞ ትግል መሪዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም አካላት ጋር አንድ ላይ ስብሰባ ይቀመጣሉ። የግብዣ እና የአቀባበል ሥነ-ሥርዓቶች ላይ ይገኛሉ። ፎቶም ይነሣሉ። እኒሁ የኮሚቴ አባላት ከግንቦት 7 መሪ ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋም ሆነ ከአክቲቪስት ታማኝ በየነ ጋር የተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ፎቶ ተነሥተዋል። ይኸው ትናንት እንኳ ኡስታዝ አቡበከር ከታማኝ በየነ ጋር በደሴ ታላቅ ሕዝባዊ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ታዲያ ከጃዋር ጋር የተነሡት ፎቶ ሌላ ምን ትርጉም ሊኖረው ይችላል? ምንም!
.
ደግሞስ አሕመዲን ብቻ ነው እንዴ አብሮ የተነሣው? በወቅቱ ደሴ ያፈራችው ኡስታዝ አቡበክርም ሆነ ጉራጌ ያፈራችው ኡስታዝ አሕመድ ሙስጠፋ አብረው ነበሩ። እነሱንም በኦነግነት ሊከሷቸው ይሆን?
.
ይሄ ሁሉ የሚሠነዝሩትን ውንጀላ ሲታይ መሰል በሚል መረጃ እንኳ ለማስደገፍ ያልቻሉ የሰነፍ አሉባልተኞች እና የዘረኛ አክቲቪስቶች ውንጀላ ነው። ቢጨምቁት ስንጣሪ ሎጂክ አይወጣውም። ሲፋቅ ባዶ ነው። ሌላው ቢቀር አገር የማፍረስ ተልእኮ ያለው ሰው እንዴት ብሎ የተነሣቸውን ፎቶዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ይበትናል? አንባቢያቸው ይህንን እንኳ ያስባል አለማለታቸው በጣም ይገርማል። ዱሮ ልጅ እያለን እንዲህ ዓይነት የተጃጃለ ነገር ሲገጥመን «የብላኔ» እንለው ነበር!
.
ልጠቅልለው… የሕዝበ ሙስሊሙን ወኪሎች ለማንቋሸሽ የምታደርጉት ጥረት በጭራሽ ዋጋ አይኖረውም። እንደውም አጀንዳችሁ አፍራሽ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ የማይሳካ ሙከራ ነው። ከወኪሎቹ ጀርባ ለዓመታት ለታገለው ሕዝበ ሙስሊም ያላችሁን ንቀትም ያሳያል። የሐሰት ፕሮፓጋንዳ አገር ለማፍረስ የሚደረግ ጡብ ማቀበል በመሆኑ ከርካሽ ዘመቻችሁ ብትቆጠቡ ይሻላል። አልያ ግን ጸባችሁ ከሕዝቡ ጋር እንጂ ከወኪሎቻችን ጋር ብቻ አይሆንም! እናም እጃችሁን ከወኪሎቻችን ላይ አንሡ!
.
Tags: #አሕመዲንጀበል #የሐሰትውንጀላ #ሐሰት #ውሸት #የሐሰትፕሮፓጋንዳ #አሉባልታ #ኢትዮሙስሊም

Latest News

video image video image video image Read More

Get Connected

logo link youtube logo link twitter logo link facebook

Contact Information