Ethiopia: በኢሰሀቅ እሸቱ የኦህዴድ (ኦዴፓ) የለውጥ ጉዞ እና አካታችነት አካታችነትን መዘንጋት ሕዝባዊ ድጋፍን ይሸረሽራል!

People in meeting
ተፃፈ በጋዜጠኛ ኢስሐቅ እሸቱ
የቀድሞው ኦሕዴድ የአሁኑ ኦዴፓ አዳዲስ ለውጦችን አስተዋውቋል። በርካታ በፖለቲካው ዓለም የቆዩ አባላቶችን በክብር በጡረታ ሸኝቷል። አዳዲስ ወጣቶችን ወደአመራር ማምጣቱን እና ለመሠረታዊ ለውጥ እንደሚሠራም ገልጿል። ይህም ብቻ አይደለም… የዓርማና የመዝሙር ለውጥ እንኳን ማድረጉን አስታውቋል። ሁሉም ደስ የሚሉ ለውጦች ናቸው። በተለይም የቆዩ አባላቱን መሸኘቱ ለሪፎርም አጀንዳው ጥሩ ማሳለጫ ስለሚሆነው የሚበረታታ ነው።
ወደአካታችነት ስንመጣ ግን ኦዴፓ ዘመኑን ያልዋጀ እና ያልተጠበቀ ሥራ መሥራቱ ቅሬታ ፈጥሯል። 9 አባላት ባሉት የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ውስጥ አንድም ሙስሊም የለም። (ምሥራቃዊውን የኦሮሚያ ክፍል እንደማኅበረሰብም ጭምር አለማካተቱ ከጥንታዊው የገዳ ሥርዓት መርህ ያፈነገጠ በመሆኑ የተነሣበትን ተቃውሞ ወደጎን ትተነው) የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከግማሽ በላይ ሙስሊም እንደመሆኑ መጠን እንዴት ይህን ዓይነት ሥራ እንደተሠራ ለእኔ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። ኦዴፓ የአካታችነት ጉዳይ አያሳስበውም ማለት ነውን? እንዴትስ ነው በተለይ ሙስሊም በሚበዛባቸው የኦሮሚያ ክልሎች የሕዝቡን መተማመን (vote of confidence) የሚያገኘው? በግሌ የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ እጅግ በማከብራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ (PM Dr. Abiy Ahmed) እና በለውጡ ጀግና በኦቦ ለማ መገርሳ የሚመራ መሆኑ ያስደሰተኝን ያክል የአካታችነት ሁኔታው ግን ትልቅ ጥያቄ ፈጥሮብኛል። .
——— ለምን አካታችነት? ——— .
አካታችነት ከብዝኀነት የመነጨ ሐብትን እንድንጠቀም፣ ከውክልና የመነጩ የፖለቲካ ችግሮችንም ቀድመን እንድንፈታ የሚያስችለን ፖለቲካዊ ባሕሪ ነው። አካታችነት የጎደለው ፖለቲካ ሁልጊዜም አንካሳ ነው። «ጥንካሬ በልዩነት እንጂ በአንድ ዓይነትነት አይደለም» እንዲል ታላቁ የራስ ማዳበር ጥበብ ባለሙያ ስቴፈን አር ኮቬይ ብዝኀዊ ሐብትን ያልተላበሰ ፖለቲካዊ ሥራ ጥንካሬን ይሰለባል። ሕዝባዊ ተቀባይነትን ይነፈጋል። .
ይህ ብቻም አይደለም። ብዝኀነትን በአካታችነት መርህ ጥቅም ላይ ያላዋለ ፖለቲካ ከቋሚ የማኅበረሰቦች ባሕሪና መገለጫ ስለሚያፈነግጥ ዘላቂ ለውጥን ሊያመጣ አይችልም። እስከ 2012 ከስኬታማ እና ተወዳጅ የቻይና ፖለቲከኞች አንዱ የነበረው ሑ ጂንታው በአንድ ወቅት «ብዝኀነት የሁሉም ማኅበረሰቦች መሠረታዊ ባሕሪ ነው። ዓለማችን ሕያው እና ተለዋዋጭ ሁናቴን እንድትላበስ የሚያደርግ ቁልፍ መሥፈርት ነው» ሲል ተናግሮ ነበር። እውነትም ነው። ከብዝኀዊነት የመነጨ አካታችነትን የተነፈገ ፖለቲካ አገርን ብዙ አያራምድም። .
እኒህን ችግሮች የማስተካከሉ ኃላፊነት ኦዴፓ ትከሻ ላይ ወድቋል። የቲምለማ ቡድን እስከዛሬ የፈጠራቸውን እና እየፈጠራቸው ያላቸውን መልካም ተጽእኖዎች በአካታችነት እጥረት እንዳይነፈግ እና በለውጥ አሿሪነት የገነባው መልካም ስም እንዳይጎድፍ በግሌ ትልቅ ሥጋት አለኝ። ይህን ሥጋት የሚጋራኝ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍል እንደሚኖርም አልጠራጠርም። .
የምናከብራችሁ የለውጥ መሪዎቻችን ሆይ…! አካታችነትን የዘነጋችሁ ቀን ሕዝባዊነታችሁ ይሸረሸራል። መሬት ላይ ለምታሳኩት ለውጥ ግብዓት የሚሆን የሕዝብ ጫንቃ ያሳጣቸኋል። ደክማችሁ የገነባችሁትን ተዓማኒነት ያፈርስባችኋል። ዛሬ ፖለቲካዊ ሥልጣን ክፍፍል ላይ ያገለላችሁት የማኅበረሰብ ክፍል የነገ ራስ ምታታችሁ ሆኖ የውድ አገራችን የነፃነት ግስጋሴ እንዳይገታ በጊዜ እወቁበት። አልያ ግን ወደትክክለኛ ሥልጣን ያወጣችሁን ሕዝባዊ ኃይል ነገ ከጎናችሁ እንዳታጡት ያሠጋል። ልብ ያለው ልብ ይበል! . .
Tags: #ኦሕዴድ #ኦዴፓ #አካታችነት #ብዝኀነት #ሕዝባዊነት #ቲምለማ #ቄሮ #ኢትዮሙስሊም
Get Outlook for iOS

Latest News

video image video image video image Read More

Get Connected

logo link youtube logo link twitter logo link facebook

Contact Information