Ethiopia: በጭቆናው ዘመን ውስጥ ተቀርቅሮ የቀረው «ሠላምታ» መጽሄት

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሕዝበ ሙስሊሙ ሐጃጆች ላይ ሲያደርስ የቆየውን በደል ስንዘረዝር ከርመናል። ለዛሬ ደግሞ ሌሎች አሥተዳደራዊ በደሎች ላይ እናተኩር።
እንደሚታወቀው የትኛውም አገራዊ ተቋም በኅትመት ሥራዎቹ ሚዛናዊነትን ማንጸባረቅ፣ ሁሉንም ማኅበረሰብ የሚወክሉ እሴቶችን እና ቅርሶችን ለተመልካች እያቀረበ አገርን ማስተዋወቅ ይጠበቅበታል። ይህንን ሲያደርግ ደግሞ አንድን እምነት ወይም ብሔር ወይም አመለካከት ብቻ መርጦ በማውጣት እና በማስተዋወቅ ሳይሆን ሁሉንም በየተራ በማሳየት፣ በማስተዋወቅ፣ ብዝኀነታችንን በማንጸባረቅ መሆን አለበት። ይህ የትኛውም የሠለጠነ እና በዴሞክራሲ የሚያምን ዜጋ የሚቀበለው የሠለጠነ መርህ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ (Ethiopian Airlines) ለበርካታ አሥርት ዓመታት አገልግሎቱን ለሚጠቀሙ ሁሉ ሲያቀርበው የቆየው #ሠላምታ የተሰኘ መጽሄት አለው። (Selamta Magazine) መጽሄቱ ከበፊትም ጀምሮ ለዓለም አቀፍ የአየር መንገዱ ተጠቃሚዎች አገሪቱንም ሆነ የአየር መንገዱን አገልግሎቶች ለማስተዋወቅ በሚል ዓላማ የሚታተም በመሆኑ በከፍተኛ የኅትመት ጥራት እና ጥንቃቄ የሚዘጋጅ ነው። ጥራት ያላቸው ፎቶዎችና የፈጠራ ችሎታ የሚታይባቸው አዘጋገቦች የመጽሔቱ መገለጫዎች ናቸው።
.
«ሠላምታ» መጽሄት የሚጎድለው አንድ ትልቅ ነገር ግን አለ — ብዝኀዊነት! መጽሄቱ አገሪቱ ውስጥ ያለውን የሃይማኖት (እና በተወሰነ መልኩም የባሕል) ብዝኀነት ለማንጸባረቅ ምንም ሲሞክር አይታይም። ኢትዮጵያን በአንድ ዓይነት ምሥል ሸብቦ ለዓለም አቀፍ ተጠቃሚዎቹ በማስተዋወቅ የአገር ገጽታን እያጓደለ ቆይቷል። ይህ ደግሞ ከሥልጣኔ እና ከዴሞክራሲ እሴቶች ጋር የሚቃረን ትልቅ ብሔራዊ ወንጀል ነው።
አንድ ሙስሊም ኢትዮጵያዊ «ሠላምታ» መጽሔትን ገልጾ ሲያገላብጥ በገጾቹ መካከል ራሱን አያገኝም። እምነቱ እና ባሕሉ ተወክሎ ሲተዋወቅ አያይም። ሃይማኖቱ እና እሴቶቹ የአገሪቱ እሴቶች አንድ አካል ተደርገው ሲንጸባረቁ አይመለከትም። እናም ቅሬታ ይሰማዋል። ሊሰማውም ተገቢ ነው። የአገሪቱ ግማሽ የሆነው ሙስሊም ማኅበረሰብ እሴት የአገሪቱ እሴት አካል አይደለምን? ኢትዮጵያ የምትወከለው በክርስትያናዊ እሴቶች እና ቅርሶች ብቻ ነውን? ስለምንድነው «ሠላምታ» መጽሔት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለኢትዮጵያ የተጓደለ ገጽታ እንዲያቀርብ የሚፈቀድለት? ስለምንድነው በከፍተኛ በጀት የሚንቀሳቀስ ፕሮፌሽናል መጽሔት አንድን ማኅበረሰብ ያገለለ ሥራ እንዲሠራ መንገድ የሚመቻችለት?

አጭር ማሳያ
በፈረንጆች አቆጣጠር ከጁላይ 2012 ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ያሉትን 37 እትሞች እንደናሙና ለማየት ተሞክሯል። (ድረ ገጹ ላይ አርካይቭ {ዶሴ} የሚጀምረው ከ2012 መሆኑን ልብ ይሏል!) ከ37ቱ እትሞች ውስጥ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ቅርስ የቀረበው በ2014ቱ የጁላይ—ኦገስት እትም ላይ ብቻ ነው። የቀረበውም የሐረር ከተማ ሲሆን በጃንዋሪ—ፌብሩዋሪ 2018 እትሙ ላይ ሐረር በድጋሚ በፎቶ ወጥቷል። በተጠቀሱት ዓመታት ሌላ የሙስሊሙንም ሆነ ከኦርቶዶክስ ውጭ ያሉ ሃይማኖቶችን እሴት የሚያንጸባርቅ ቅርስ/መገለጫ/የአምልኮ ቦታ/የአምልኮ ሥርዓት የሚያሳይ ነገር አልቀረበም። (ሌላው ቀርቶ የሙስሊም በዓላት አከባበር እንኳ አልቀረበም!)
በሌላ በኩል ግን የኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻችን እሴቶች/ቅርሶች/የአምልኮ ሥርዓቶች በሰፊው ቀርበዋል። (በመቅረባቸውም ቅሬታ ያለው ማንም ሰው የለም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቅርሶች ልክ እንደሌላው ሃይማኖት ቅርሶች ሁሉ የአገር ሐብት በመሆናቸው በሠላምታም ሆነ በሌላ ኅትመት መቅረባቸው ችግር የለውም። ነገር ግን የትኛውም የሠለጠነ ሰው እንደሚስማማው ለሌሎች ሃይማኖት ቅርሶችም ተመጣጣኝ እድል መሰጠት አለበት። ከታች የቀረበው ንጽጽርም «ለምን የኦርቶዶክስ ቅርሶች ቀረቡ?» በሚል ሳይሆን «ለምን የሌሎች ሃይማኖቶች እሴት ተመጣጣኝ ቦታ አይሰጠውም?» በሚል መንፈስ የተዘጋጀ ነው።)
ለንጽጽር ብናይ ከ2012 ጀምሮ ባሉት 37 የ«ሠላምታ» መጽሄት እትሞች የሚከተሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅርሶች/እሴቶች/የበዓል አከባበሮች ቀርበዋል:—

 • በማርች—አፕሪል 2013 እትም ደብረዳሞ እና ላሊበላ አብያተ ክርስትያናት፤
 • በጃንዋሪ—ፌብሩዋሪ 2014 እትም ላሊበላ አብያተ ክርስትያናት፤
 • በኖቬምበር—ዲሴምበር 2014 እትም የጥምቀት በዓል አከባበር፤
 • በሜይ—ጁን 2015 እትም የመስቀል በዓል አከባበር፤
 • በጃንዋሪ—ፌብሩዋሪ 2017 እትም የገና በዓል አከባበር፤
 • በጃንዋሪ—ፌብሩዋሪ 2018 እትም የላሊበላ አብያተ ክርስትያናት፤
 • በማርች—ኤፕሪል 2018 እትም አቡነ የማታ ገዳም፣ አባ ገሪማ ገዳም፣ አብራሓ አጽብሓ ገዳም እና ደብረ ዳሞ ገዳም፤
 • ከባሕል ጋር በተያያዘ ደግሞ በተለምዶ ሰሜናዊ የሚባለውን ማኅበረ ፖለቲካ የሚያንጸባርቁ ሥራዎች በተጠቀሰው ወቅት እንደሚከተለው ቀርበዋል:—
 • በሴፕቴምበር—ኦክቶበር 2014 እትም አጼ ምኒልክ እና አገዛዛቸው፤
 • በጃንዋሪ—ፌብሩዋሪ 2015 እትም የጎንደር እና ፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት፤
 • በጃንዋሪ—ፌብሩዋሪ 2018 እትም በድጋሚ የፋሲለደስ አብያተ መንግሥታት፤

እንግዲህ በድረ ገጹ አርካይቭ የተቀመጡት የመጽሄቱ እትሞች ያለፉት 6 ዓመታት ብቻ እንደመሆናቸው በንጽጽር የቅርብ ጊዜ ናቸው። ከ2012 ወደኋላ በሄድን ቁጥር ከሃይማኖት አንጻር አካታች የመሆን እድላቸው የበለጠ እየቀነሰ መሄዱ አይቀርም። እንደናሙና ካየነው ከ37 እትም ውስጥ ይህንን ያክል መበላለጥ በምንም መልኩ ተገቢ ሊሆን አይችልም። ቢያንስ ከሙስሊሙ በዓላት የአንዱን አከባበር እንኳ እንዴት አያሳይም? አገር የጋራ ሆኖ ሳለ ስለምን ቅርሶቻችን፣ እሴቶቻችንን፣ ሃይማኖታዊ በዓላቶቻችንን አያስተዋውቅም? ስለምን የአገርን ገጽታ ያጓድላል? የ«ሠላምታ» መጽሄት አዘጋጆች እና አለቆቻቸው እንዴት ራሳቸውን እንደባለሙያ ጋዜጠኛ እንደሚቆጥሩ እንጃ!
አንድ ነገር ግልጽ ነው…! አገራችን የምታምረው ሁላችንም ስንኖርባት ነው። ኢትዮጵያዊ እሴቶች የሚዳብሩት የሁላችንም እሴቶች የአገር ገጽታ ግንባታ ግብዓት ሲሆኑ ነው። «ሠላምታ» መጽሄት ባለፉት የሃይማኖታዊ ጭቆና ዘመናት ውስጥ ተቀርቅሮ የቀረ መሆኑ ፍትሕ ፈላጊ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ሊያሳዝን የሚገባ ጉዳይ ነው።

 • አየር መንገዱ በሐጅ ተጓዦች ላይ የሚያደርሰው የአገልግሎት በደል (የበረራ ፕሮግራም መረጃ ክልከላ፣ በረራ ስረዛ፣ ምግብ እና ማረፊያ ክልከላ፣ ማመናጨቅ እና ማጉላላት) በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን፤
 • አየር መንገዱ በሐጅ ትኬት ክፍያ ላይ እጥፍ ዋጋ በመጨመር የሚያንጸባርቀውን ግልጽ መድልዎ በማስወገድ በሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ሃይማኖታዊ ጉዞ ወቅት የሚያደርገውን ታላቅ ቅናሽ እና ልዩ መስተንግዶ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፤
 • አየር መንገዱ «ሠላምታ» መጽሔትን በመሣሠሉ የአገር ማስተዋወቂያ የኅትመት ሥራዎቹ ላይ የሚያንጸባርቀውን የሃይማኖት መድልዎ በማቆም ሙስሊሙንም ሌላውንም ኢትዮጵያዊ እምነት፥ ባሕል እና ቅርስ በሚያንጸባርቅ መልኩ እንዲያስተካክል እንጠይቃለን
  ይህንን ጽሑፍ ሼር በማድረግ እና ሐሽታጎቹን ተጠቅሞ በገጽዎ አስተያየትዎን በማሥፈር የሚዛናዊ እና ሥልጡን ዜጋ ኃላፊነትዎን እንዲወጡ እንጋብዛለን!

#ShameOnEthiopianAirlines #Hajj2018 #በአየር_መንገዳችን_አፍረናል

Latest News

video image video image video image Read More

Get Connected

logo link youtube logo link twitter logo link facebook

Contact Information