Ethiopia: የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ተቃውሞ እና አገራዊ ፋይዳው፤ አጭር ቁዘማ

(ስደተኛው መስፍን ነጋሽ፤ ከአገረ ስዊድን)

ላለፉት ሰባት ወራት በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ምህዳር (public sphere) ሳይበርዱ ከሰነበቱት ርእሰ ጉዳዮች አንዱ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ያነሱት የመብት ጥያቄ እና መንግሥት ለጥያቄው የሰጠው ትርጉምና ምላሽ ይገኝበታል። ነገሩ ሰሞኑን ተካሮ ሰንብቷል። የመነጋገሪያ አጀንዳነቱም እንዲሁ በጣም ጨምሯል። በዚህ ንግግር ውስጥ በስሕተትም በእቅድም እየተምታቱ የሚቀርቡ ጉዳዮች መኖራቸውን ብዙዎች ያስተውሉታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሆኖም ጉዳዮቹን ነቅሶ ማውጣቱ ለውይይት ብቻ ሳይሆን አቋምን ለመፈተሽም ይረዳል በሚል እምነት ነገሩን ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። ነገሩ ብዙ ጉዳዮችን የሚያሰናስል እንደመሆኑ ቁዘማዬም (reflection) ጥቂት ረዝሞ ልታገኙት ትችላላችሁ። ትእግስታችሁን እማጸናለሁ።

በዚህ ጽሑፍ የኢትዮጵያውን ሙስሊሞች ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄዎች በሁለት ምክንያቶች በሌላውም ኢትዮጵያዊ መደገፍ አለባቸው እላለሁ። ሕጋዊ ጥያቄዎቹ ”ከአክራሪነት/ሽብርተኝነት” ጋራ ተደባልቀውና ተምታተው እየቀረቡ ችላ መባልም ሆነ መረገጥ አይገባቸውም ስል እከራከራለሁ።

የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ተቃውሞ እና አገራዊ ፋይዳው፤ አጭር ቁዘማ
I am at Awelia because injustice is there!

(ስደተኛው መስፍን ነጋሽ፤ ከአገረ ስዊድን)

ላለፉት ሰባት ወራት በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ምህዳር (public sphere) ሳይበርዱ ከሰነበቱት ርእሰ ጉዳዮች አንዱ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ያነሱት የመብት ጥያቄ እና መንግሥት ለጥያቄው የሰጠው ትርጉምና ምላሽ ይገኝበታል። ነገሩ ሰሞኑን ተካሮ ሰንብቷል። የመነጋገሪያ አጀንዳነቱም እንዲሁ በጣም ጨምሯል። በዚህ ንግግር ውስጥ በስሕተትም በእቅድም እየተምታቱ የሚቀርቡ ጉዳዮች መኖራቸውን ብዙዎች ያስተውሉታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ሆኖም ጉዳዮቹን ነቅሶ ማውጣቱ ለውይይት ብቻ ሳይሆን አቋምን ለመፈተሽም ይረዳል በሚል እምነት ነገሩን ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። ነገሩ ብዙ ጉዳዮችን የሚያሰናስል እንደመሆኑ ቁዘማዬም (reflection) ጥቂት ረዝሞ ልታገኙት ትችላላችሁ። ትእግስታችሁን እማጸናለሁ።

በዚህ ጽሑፍ የኢትዮጵያውን ሙስሊሞች ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄዎች በሁለት ምክንያቶች በሌላውም ኢትዮጵያዊ መደገፍ አለባቸው እላለሁ። ሕጋዊ ጥያቄዎቹ ”ከአክራሪነት/ሽብርተኝነት” ጋራ ተደባልቀውና ተምታተው እየቀረቡ ችላ መባልም ሆነ መረገጥ አይገባቸውም ስል እከራከራለሁ።

እንደ መነሻ። በዚህ ርእሰ ጉዳይ ዙሪያ ስድስት አይነት የአመለካከት ፈርጆችን ተመልክቻለሁ። የመጀመሪያው ብዙዎቻችን የምንደግፋቸውና ሕጋዊ ጥያቄ እያነሱ የሚገኙት ሙስሊሞች ናቸው። ሁለተኛዎቹ በእምነታቸው ሙስሊም ቢሆኑም ጥያቄዎቹን ወይም/እና ጠያቂዎቹን በጥርጣሬ የሚመለከቱ ናቸው። ሦስተኛዎቹ በእምነታቸው ሙስሊም የሆኑ/ያልሆኑ፣ የሙስሊሞችን ሕጋዊ ጥያቄዎች በዴሞክራሲና አብሮ በመኖር መርህ ብቻ የሚደግፉ ናቸው። አራተኛዎቹ የሌላ እምነት ተከታዮች ሲሆኑ የሙስሊሞችን ጥያቄዎች በከፍተኛ ጥርጣሬ የሚመለከቱ፣ የሙስሊሞችን እንቅስቃሴ በአብዛኛው ከአክራሪነት ጋራ በማያያዝ በስጋት የሚከታተሉ ናቸው። እነዚህ የሚበዙት ወገኖች ሁል ጊዜም መንግሥት ሁሉንም ነገር እንዲቆጣጠርላቸው ስለሚፈልጉ የሙስሊሞች መብት መከበር ቀዳሚ ጉዳያቸው አይደለም። ከሞላ ጎደል መንግሥትን ባይደግፉ እንኳን አይቃወሙም፤ የመንግሥት እንዲሁም ስለጉዳዩ ”ያስተምራሉ” የሚባሉ የሃይማኖት ሰባኪዎቻቸው የፕሮፓጋንዳ ኢላማዎች ናቸው። አምስተኛው አመለካከት የገዢውን ፓርቲ ሥልጣንና ጥቅም ለማረጋገጥ የትኛውንም አይነት ትንተናና ማስረጃ የሚጠቀሙ ናቸው። ስድስተኛዎቹ የመንግሥት ተቃዋሚዎች የሆኑ የተደራጁ ቡድኖች ናቸው። እነዚህ ወገኖች የሙስሊሞችን የመብት ጥያቄዎች መንግሥትን ለማጣጣል እና ለማዳከም ተጨማሪ ማሳያ ከተቻለም መሣሪያ ለማድረግ የሚፈልጉ ናቸው፤ ጉዳዩን የሚያቀርቡበትና የሚደግፉበት ርቀት እንደ ቡድኖቹ አቅምና ዓላማ ይለያያል። አንዳንድ አስተያየቶች ከአንድ በላይ በሚሆኑ ምድቦች ውስጥ ሊወድቁ ወይም ሌላ የራሳቸው ምድብ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ መጠርጠር አይጎዳም።

የአወሊያ እና የአራት ኪሎ አጀንዳዎች

በአወሊያ ትምህርት ቤት የተጀመረው ”ቀላል” የአስተዳደራዊ ፍትሕ ጥያቄ እዚህ ይደርሳል ብለው ያሰቡ ብዙ አልነበሩም፤ ከነበሩ። ለማንኛውም ጥያቄው አድጎ አሁን ሁለት አንኳር ጉዳዮች ነጥረው ወጥተዋል።

1. መንግሥት በሃይማኖትና በአስተዳደር ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እንዲያቆም የመጅሊሱን የተቋማዊ ነጻነት እንዲያከብር መጠየቅ
2. የመጅሊሱን አመራር በሕዝብ በተመረጡ ወኪሎች የመተካት አፋጣኝ ጉዳይ

ለውይይት እንዲመች እነዚህን ሁለት አንኳር ጥያቄዎች ”የአወሊያ ጥያቄዎች” በሚል እንጥራቸው። እነዚህ አጀንዳዎች በወቅቱ ቢያንስ በአዲስ አበባ የሚገኙ፣ በተለይም በየሳምንቱ በአወሊያ መሰባሰብ የጀመሩት ቆይቶ ደግሞ አብዛኞቹ ሙስሊሞች ከሞላ ጎደል ያለልዩነት የሚጋሯቸው ወደ መሆን አድገዋል። ጥያቄዎቹ በመሠረቱ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ሙስሊሞችን (በቀጥታም በተዘዋዋሪም) የሚመለከቱ እንደመሆናቸው መጠኑ ቢለያይም ሁሉም በየአካባቢው በግልም በጋራም በነገሩ ላይ አቋም መውሰዱ የማይቀር ነበር። የአወሊያው እንቅስቃሴ ሲብላሉ የቆዩትን ቅሬታዎችና ጥያቄዎች መልክና ቅርጽ ሰጥቶ ለማቅረብ መነሻ ከመሆኑ በቀር ችግሮቹ የከረሙ ለመሆናቸው ባለቤቶቹ በእርግጠኝነት ያናገራሉ። በተጨማሪም የአወሊያው እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት መንግሥትና የመጅሊሱ አመራሮች የሕዝበ ሙስሊሙን አትኩሮት የሚስቡ እርምጃዎችን/አቋሞችን ሲወስዱ ነበር፤ ከእነዚህም ዋናዎቹና ዘላቂ ውጤት ያስከተሉት አጅንዳዎች የሚከተሉት ናቸው።

1. ዋሐቢዝም/አክራሪነት እና ስጋቱ። መንግሥት በአክራሪነት የሚከሳቸውን ”የዋሐቢዝም” ተከታዮች ማሳደድ እና በአደባባይ መክሰስ መጀመሩ፤ እንዲሁም በአስተምህሮቱ ምንነትና ተግባራዊ መገለጫዎች ላይ ቁርጥ ያለ መግባባት አለመኖሩ የፈጠረው ውዥንብር የሰሞኑ ተዋስኦ አንድ ወሳኝ ግብአት ነው። ይህ ከእስልምና እምነት ተከታዮች ውጭ ያሉት ዜጎች የያዙትን ግንዛቤና የተፈጠረባቸውን ስጋት ይጨምራል።

2. አሐበሽ። በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መሆኑ የሚነገረውን ”አክራሪነት ወይም ዋሐቢዝምን” ”ለመቆጣጠር ይጠቅማል” በሚል መንግሥት ”አ(ል)ሐበሽ” የተባለው አስተምህሮ የበላይነት እንዲያገኝ በግልጽ ድጋፍ ማድረጉ፤ ይህን አንቀበልም ያሉትን ”ማስገደድ ሞክሯል” የሚለው ዜና በስፋት መዛመቱ የልዩነት በሕዝበ ሙስሊሙና በመንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት ወደ አዲስ ደረጃ አሸጋግሮታል። ”መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ መግባቱን ያቁም” የሚለው የአወሊያ ጥያቄ (1) አንዱ የቅርብ መነሻም ይህ ጉዳይ ሆኗል።

3. መንግጅሊስ። መንግሥት በርእዮተ ዓለማዊ ግቡ የተነሣ መጅሊሱን የመቆጣጠር ለድርድር የማያቀርብ ፍላጎት አለው።ከዚህም ጋራ ተያይዞ የመጅሊሱ አመራር በአወሊያ ጥያቄዎችና በሌሎችም ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ጎን መቆሙ እና መንግሥትም በተራው መጅሊሱን እስከመጨረሻው መደገፉ የከረመ አኗኗር ነው። ፌደራል ጉዳዮችና መጅሊሱ አንዱ በአንዱ ውስጥ የጠፉ የመሰሉባቸውን አጋጣሚዎች ልብ ይሏል። መንግሥት በኦርቶዶክስና በሌሎቹም አስተዳደር ውስጥ ቀጥኛ ቁጥጥር እንዳለው ሁሉ የመጅሊሱ አዲስ ቅኝት ባይሆንም አንድ ሚኒስትር፣ ለዚያውም የሌላ እምነት ተከታይ፣ በእስልምና ውስጥ ካሉት አስተምህሮዎች ”ይህኛውን መቀበል አለባችሁ፤ ያኛው አይበጃችሁም” ብሎ በአደባባይ መመሪያ ሲያስተላልፍ ግን ተሰምቶ አይታወቅም ነበር። ጥያቄ አቅራቢዎቹ ”መንግጅሊስ” የሚባለው ሕገ ወጥ ጋብቻ ፈርሶ ሁለቱም ወደ ቀደመ ጉርብትናቸው ይመለሱ ባዮች ናቸው። የመንግጅሊሱ አባላት ግን አንድ ቤት አብረን ማደር ብንጀምርም አልተጋባንም፤ እርቃን ብንተያይም አንሶላ የመጋፈፍ ፈተናውን ተቋቁመናዋል እያሉን ነው።

እነዚህን ሦስት (አሐበሽ፤ ዋሐቢዝም/አክራሪነት፤ መንግጅሊሱ) ጉዳዮች ”የአራት ኪሎ አጀንዳዎች” ብለን እንጥራቸው። ”የአራት ኪሎው” ስል ግን መንግሥት በቀጥታ በባለቤትነት/በአድራጊነት የገባባቸው ለማለት እንጂ ሕዝበ ሙስሊሙንም ይሁን ሌላውን ሕዝብ አይመለከቱም ማለት አይደለም። ሁሉም ዜጋ በግሉም ሆነ በተለያዩ ሌሎች ቡድናዊ ፍላጎቶች/ግንዛቤዎች መነሻነት በእነዚህ ሦስት አጀንዳዎች ላይ የራሱን ግንዛቤና አቋም መውሰዱ የማይቀር ነው።

የአወሊያ እና የአራት ኪሎ አጀንዳዎች የተለያዩ ይሁኑ እንጂ የተሰናሰሉም ናቸው፤ አንዱን አጀንዳ ሲነኩት ሌላው ይተረተራል። ለዚህ ነው ነገሩን ለመረዳት አጅንዳዎቹ የሚለያዩበትን እና የሚገናኙበትን ስስ ብልት በጥንቃቄ መመልከት የሚገባው። የአወሊያ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ሲጠየቅ ስለአክራሪነት በማንሳት ነገሩን ሙሉ በሙሉ ለመደባለቅ የሚሞክሩት መንግሥትና ደጋፊዎቹ የሚፈጥሩትን ውዥንብር ለማጥራት አጋጣሚው ጥሩ ነው።

ሃይማኖትን ከፖለቲካው መለየት

የወቅቱ የሙስሊሞች እንቅስቃሴ በተነሣ ቁጥር ተደጋግሞ የሚደመጠው የፖለቲካ አጀንዳ ጉዳይ ነው። የአገራችን መንግሥታትና ስር የሰደደው ድንቁርና የተከሉብን ፖለቲካን አጥብቦ፣ አጣሞና አጨልሞ ብቻ የመረዳት በሽታ የሚያስከትለውን የአመለካከት ችግር ለመረዳት ነገሩ ጥሩ ማሳያ ነው። መንግሥትም ይህንኑ የግንዛቤ መምታታ እየተጠቀመበት ነው።

የዚህ መምታታት ሰለባ ከመሆን ለማምለጥ በመጀመሪያ መመለስ ያለበት አንድ ጥያቄ አለ፤ ”አንድ ጉዳይ ሃይማኖታዊ ወይም/እና ፖለቲካዊ የሚሆነው መቼ ነው?” የሃይማኖት እና የመንግሥት ግንኙነት የፖለቲካ ጉዳይ መሆኑን ለማረጋገጥ ከሕገ መንግሥቱ የበለጠ እማኝ መጥራት አያስፈልግም። ሕገ መንግሥቱ ስለሃይማኖቶች ዶክትሪን አያወራም፤ ነገሩ የፖለቲካ ጉዳይ አደለምና። ሆኖም ሕገ መንግሥቱ ”መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም፤ ሃይማኖት በመንግሥት ውስጥ ጣልቃ አይገባም” በማለት የሁለቱን ግንኙነት ጥንቱኑ የፖለቲካ ጉዳይ አድርጎታል። አንዱ በሌላው ውስጣዊ ጉዳይ በሕግ ከተደነገገው ውጭ ጣልቃ መግባቱም ሆነ አለመግባቱም ፖለቲካ ነው። ጣልቃ መግባት ሕገ ወጥ የፖለቲካዊ እርምጃ ነው፤ ጣልቃ አለመግባት ደግሞ ሕጋዊ የፖለቲካ ተግባር ነው።

እጅግ ወግ አጥባቂ በሆነ ትርጉም አንድ ጉዳይ መንግሥት እና ዜጋ/ዜጎች የሚገናኙበት ከሆነ ደረጃው ቢለያይም ፖለቲካዊ ይሆናል። ጉዳዩ እንደይዘቱ በአስተዳደራዊ እርምጃ ወይም በፖሊሲ/ሕግ ሊስተናገድ የሚገባው ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ”ትክክለኛው የእስልምና/ክርስትና አስተምህሮ የትኛው ነው?” የሚለው ጥያቄ ሲጀመር የግለሰብ አማኙ ከዚያ ካለፈ ደግሞ የእምነት ተከታዮቹ የቡድን ጉዳይ ነው። በዚህ ቅርጹ ጉዳዩ ፖለቲካዊ አይደለም። መንግሥት እዚህ ውስጥ ገብቶ ማብራሪያ ሲሰጥ፣ አቋም ሲወስድ ነገሩ ሕገ ወጥ ፖለቲካ ይሆናል። አንዱ ሃይማኖተኛ እምነቱን በሌላው ላይ ለመጫን ወይም ልዩነቶቹን የሌሎችን ዜጎች መብቶች በሚጥስ መንገድ ለመፍታት ሲሞክር ነገሩ የፖለቲካ ጉዳይ ይሆንና የመንግሥትን ተሳትፎ ግድ ይላል። ምክንያቱም መንግሥት መብታቸው የተጣሰ ዜጎቹን መብት ለማስከበር ጣልቃ የመግባት ሕጋዊ ግዴታ ስላለበት ነው፤ መብቱ ለተጣሰበት ዜጋ/ቡድን አስተምህሮ አድልቶ ግን አይደለም። አንድ የሃይማኖት አስተምህሮ በራሱ አባሎችም ላይ ይሁን በአጠቃላይ በማኅበረሰቡ ላይ የደኅንነት ስጋት የሚፈጥር ከሆነም እንዲሁ መንግሥት ጣልቃ የመግባት መብት ብቻ ሳይሆን ግዴታም አለበት። በዚህ ሁኔታም ቢሆን ግን መንግሥት ጣልቃ የሚገባው አስተምህሮቱ ካለው መለኮታዊ/መንፈሳዊ ዋጋ አንጻር አይደለም፤ የፖለቲካ ማኅበረሰቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ብቻ ነው።

ዜጎች በሕግ የተረጋገጠላቸው መብትና ነጻነት እንዲከበር ሲጠይቁ ጥያቄው ደረጃው ቢለያይም የፖለቲካ ጥያቄ ከመሆን አያመልጥም። አንድም ይሁን መቶ ሺህ አማኞች መንግሥትን ”በሃይማኖታችን ጉዳይ ጣልቃ እየገባህ ስለሆነ ተከልከል ባዋጅ” ሲሉት ነገሩ የፖለቲካ ጥያቄ እንጂ የሃይማኖት ምልጃ አይደለም። ”አመራሮቻችንን መንግሥት ሊሾምብን አይገባም፤ ራሳችን እንምረጣቸው” ብለው መንግሥትን ሲጠይቁና ሲቃወሙ ዜጎቹ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው የፖለቲካ ጥያቄ እያቀረቡ እንጂ እምነታቸውን ለማስፋፋት ሰበካ እያደረጉ አይደለም።

በአጭሩ በሕግ እውቅና የተሰጠውን መብት መጠየቅ ፖለቲካ ካልሆነ፣ ፖለቲካ የሚባል ነገር የለም ማለት ነው። መብት እንዲከበር መጠየቅም ሆነ መብት እንዲጣስ መፍቀድ የፖለቲካ አቋም ነው ብዬ አምናለሁ። ግለሰቡ ይህንን የሚጠራበት ስም ምንም ይሁን የነገሩን ፖለቲካዊነት አያስቀረውም። የችግሩ ምንጭ የፖለቲካ ጥያቄን ከፓርቲ ፖለቲካ ጋራ ማምታታት ሊሆን ይችላል። የፓርቲ ፖለቲካ በመሠረቱ ጥያቄዎቹን ተደራጅቶ የመንግሥት ስልጣን በመያዝ ጭምር ለመፍታት መፈለግን ታሳቢ ያደርጋል። ይህ ግን ብቸኛው መንገድ አይደለም። ዜጎች በፓርቲ መደራጀት ሳያስፈልጋቸው የፖለቲካ ይዘት ያለውን ጥያቄ ማቅረብ እና በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን ለማስከበር መታገል ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ፖለቲካዊ ጥያቄ አቀረባችሁ ተብለው መከሰስ የለባቸውም፤ በግልም ይሁን በቡድን ፖለቲካዊ ጥያቄ ማቅረብ ወንጀልም ስህተትም አይደለምና። ”ፖለቲካዊ ጥያቄ ማንሣት የሚችሉት ፓርቲዎች ብቻ ናቸው” የሚል የተጻፈ ሕግም ሆነ የታወቀ ስምምነት የለንም።

ሰሞኑን በአወሊያ አጀንዳዎች ዙሪያ ተቃውሞ በማሰማት ላይ የሚገኙት ሙስሊሞች ”የፖለቲካ አጀንዳ አላቸው” እየተባሉ በመንግሥትና በደጋፊዎቹ ሲከሰሱ እንሰማለን። ከምእመናኑም አንዳንዶቹ ”የፖለቲካ ጥያቄ የለንም፤ ጥያቄያችን ሃይማኖታዊ ነው” ሲሉ ለተሳሳተ ክስ የተሳሳተ መከላከያ ያቀርባሉ። ”ሕገ መንግሥቱ ይከበር” ብሎ የሃይማኖት ጥያቄ አለ እንዴ? ሕገ መንግሥቱ እኮ ቢያንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የፖለቲካ ማኅበረሰባችንን ለማስተዳደር የተስማማንበት የፖለቲካ ሰነድ እንጂ የሃይማኖት መጽሐፍ አይደለም። ሙስሊሞች ”በቅዱስ ቁርአን የተጻፈው ይከበር” በሚል ክርክር ቢለያዩ ነገሩ በሰላም እስከተካሔደ ጥያቄው የሃይማኖት ነው ሊባል ይችላል። ”መንግሥት በሃይማኖታችን ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን ያቁም፤ ሕገ መንግሥቱ ይከበር” ከማለት የበለጠ የፖለቲካ ጥያቄ ምንድን ነው? ከመንግሥትና ከሌሎችም ወገኖች የሚቀርበው ክስ ለተቃውሞ የወጡት ዜጎች ወይም መሪዎቻቸው ”የፖለቲካ ሥልጣን የመያዝ አጀንዳ አላቸው” የሚል ከሆነም ተገቢውን መልስ መስጠት እንጂ ፖለቲካዊውን ሃይማኖታዊ እያሉ መጥራት የሚያስገኘው ጥቅም የለም። ከሳሽም ”ሰዎቹ ከሕግ ውጭ በሃይማኖት ተደራጅተው የፖለቲካ ስልጣን የመያዝና እምነታቸውን በሌላው ላይ ለመጫን ይፈልጋሉ” ያለበትን ማስረጃ የማቅረብ ሸክሙ ይከተለዋል፤ ተከሳሽም የቀረበበትን ማስረጃ የሚያፈርስ ነገር ማቅረብ ይኖርበታል።

ይህን ስል ግን በኢሕአዴግ መዝገበ ቃላት ማንኛውም ይዘት ያለውን የፖለቲካ ጥያቄ ማንሳት ወንጀል መሆኑን ዘንግቼው አይደለም። የፓርቲ መሪ ሆንክ፣ ጋዜጠኛ ሆንክ፣ የሃይማኖር መምህር ሆንክ….ለውጥ የለውም። ለነገሩ ”ጥያቄያችን የፖለቲካ አይደለም” ማለት ከኢሕአዴግ አፈና የሚያስጥልና ለጥያቄ መልስ የሚያስገኝ እንዳልሆነ ሁላችንም አስቀድመን የምናውቀው ነው። ለማንኛውም የሰሞኑ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ያለውን ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ብልት በጥንቃቄ መለየት ይገባል።

አወሊያ እና አራት ኪሎ ከእንጦጦ ሲታዩ

በመላው ዓለም እየሆነ እንዳለው ሁሉ ኢትዮጵያውም ውስጥ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ዜጎች የሚያደርጓቸውን ነገሮች በደፈናው ከአክራሪነት እና አሸባሪነት ጋራ ማያያዝ የተለመደ እየሆነ ነው፤ ትክክል ነው ማለት ግን አይደለም። ከዚህ ቀደም በተወሰኑ ቦታዎች ”አክራሪ” በተባሉ ሙስሊሞች ደረሱ የተባሉ የጥፋት ድርጊቶች ለስጋቱ እንደተጨባጭ ማስረጃም ሆነው ይቀርባሉ። መንግሥትም በበኩሉ የተደራጀ የአልቃኢዳ ሴል መገኘቱን እስከመግለጽ ደርሷል።

የአክራሪነት አዝማሚያ ያለቸው ዓለም አቀፍ ቡድኖች በኢትዮጵያ ውስጥ ተጽእኖ ለመፍጠር ቢፈልጉ ወይም ይህንኑ ለማድረግ ቢሞክሩ ብዙ የሚገርም አይደለም። ሆኖም ይህንን ዓላማ የሚደግፉት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ምን ያህል እንደሆኑ፣ እነማን እንደሆኑ፣ በዚሁ መስመር እንቅስቃሴ ስለማድረጋቸውና ስለመደራጀታቸው ከታመነ ገለልተኛ ምንጭ ማረጋገጫ አልቀረበም። እንዳለመታደል ሆኖ መንግሥታችንን ጭምር በዚህ አናምነውም። ሆኖም በቅርብ የማውቃቸው ሙስሊም ወዳጆቼ ጭምር መጠኑ ቢለያይም ”የአክራሪነት” አዝማሚያ ያለቸው ትምህርቶች መስፋፋት መጀመራቸውን አይደብቁም። የሌላ እምነት በተለይም የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ዜጎችም የስጋቱ ተጋሪዎች ናቸው። በስጋት ላይ ተመርኩዞ አቋም ለመያዝ መቻኮልና መላውን ሙስሊም ከጥቂቶቹ ደባልቆ ማየቱ ግን አደገኛ ቁልቁለት ነው።

መንግሥት በሚያቀርብልን ማስረጃዎች እምነት የለንም ማለት ግን መንግሥት ተጫባጭ ስጋቶች የሉትም ማለት አይደለም። ሌላው ቢቀር ይህን ስጋት የሚጋሩ ሙስሊሞች እና ሌሎችም ዜጎች አሉ። ችግሩ የሚመጣው ስጋቶቹን ለማረጋገጥ እና ለማስወገድ በተመረጠው መንገድ ላይ ነው። የዚህ ጽሑፍ መነሻ እነዚህን ስጋቶች መዘርዘር ባለመሆኑ ወደ ክርክሩ አልገባም። ስጋቱ መኖሩ ወይም ስጋታ ያላቸው ወገኖች መኖራቸው ግን ለክርክር የሚቀርብ አይደለም። እዚህ የማነሳው ሙግት ይህ ስጋት የአወሊያ ጥያቄዎችን ለመቀልበስ ወይም ላለመደገፍ ምክንያት መሆን አይገባውም የሚል ነው።

”የአክራሪነት አዝማሚያ ያላቸው ሙስሊሞች ስላሉ በአጠቃላይ ሙስሊሞች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ሊከበርላቸው አይገባም” ብሎ ፊት ለፊት የሚከራከር ሰው አልገጠመኝም። ሆኖም ስለ አወሊያ ጥያቄዎች ሲነሳ ተሽቀዳድመው ስለ አሸባሪነት ለማስረዳት የሚግደረደሩት ወገኖች በገደምዳሜ እያሉን ያሉት ይህንኑ ነው። ለምሳሌ 10000 (ቁጥሩ ምሳሌ ነው) የሚሆኑ አሸባሪ ሙስሊሞች አሉ እንበል፤ ለክርክሩ ያህል። ይህ ማለት መንግሥት አንዱን የእስልምና አስተምህሮ ከሌላው አስበልጦ በምእመኑ ላይ ለመጫን መሞከሩ፣ ይህንንም በገንዘብና በተቋም መርዳቱ አግባብ ነው ማለት ነው? የመጅሊሱን አመራር አማኞቹ በመረጡት ሳይሆን መንግሥት በፈለገው መንገድ ማስስኬዱ ተገቢ ነው ማለት ነው? በአወሊያ በሕዝብ የተመረጡ ወኪሎችን አሸባሪ ብሎ ማሰሩ አግባብ ነው ማለት ነው? የአወሊያን ጥያቄ ያነሱትን ሙስሊም ወገኖቻችንንን የደገፍን ሌሎች ዜጎችንም ”አሸባሪነትን የሚደግፉ፣ ሐላፊነት የማይሰማቸው፣ ብጥብጥን የሚጠሩ” በሚሉ ቀልደኛ ክሶች ለማሸማቀቅ ይሞከራል። ይህ ግን ”የአወሊያ ጥያቄዎች”ን አገራዊ ፋይዳ ለማድበስበስ የሚደረግ ሙከራ ከመሆን አያልፍም።

”አሸባሪነትን” እና ”አክራሪነትን” መከላከል ተገቢ ስለመሆኑ እንስማማለን። በቃላቱ ትርጉም እና ኢትዮጵያ ውስጥ ባላቸው ተግባራዊ መገለጫ ላይ የሰከነ ውይይት አድርገን እስከተስማማን ድረስ ራሳቸው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጭምር ይህንን ለመዋጋት ቀዳሚዎቹ መሪዎች እንደሚሆኑ አልጠራጠርም። አሁንም በድጋሚ ለማስታወስ ግን የአወሊያ ጥያቄዎች ”ከአክራሪነት/አሸባሪነት” ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት የላቸውም። ጥያቄዎቹን የሚደግፉ ”በአክራሪነት” የሚጠረጠሩ ሰዎች ቢኖሩ እንኳን ብዙዎች ያነሷቸውን ሕጋዊ ጥያቄዎች ዋጋ የሚያረክሱ ሊሆኑ አይችሉም። በግሌ ጥያቄዎቹን የምደግፈው፤ ጠያቂዎቹ ላሳዩት ብስለት አክብሮቴን የምገልጸውም ከዚሁ መንፈስ በመነሳት ነው። መንግሥት ሊለን እንደሚሞክረው ቢሆን እንኳን ”በአክራሪነት” በሚጠረጠሩት ሰዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ እስካሁን ለምን እንደዘገየ ማስረዳት አይችልም። ምናልባትም ከሁሉም በላይ የአክራሪነት አዝማሚያ ያላቸውን ሰዎች በተዘዋዋሪ የሚደግፈው መንግሥት ገና ከጅምሩ የተከተለው አቅጣጫ ነው።

ሰላማዊውን ሙስሊም ሁሉ ”ለምን ተቃውምከኝ” በሚል ”አሸባሪ” ብሎ መጥራትና ማሳደድ እነዚህን ዜጎች ”አክራሪ” ወደሚባለው ጎራ ወይም በዚህ ወደሚከሰሰሱት ሰዎች የሚገፋቸው እንደሚሆን መገመት አይከብድም።
የአወሊያ ጥያቄ አስተባባሪዎች ሆነው የተመረጡት ሰዎችና ሌሎችም ኢትዮጵያን በሸርኢ የማስተዳደር ድብቅና የሩቅ ጊዜ አላማ አላቸው የሚል ክስ አለ። ይህ ስጋትና ክስ በተጨማጭ ማስረጃ መደገፍ እና በሕግ መዳኘት ይኖርበታል። እንዳለመታደል ሆኖ ሕጋዊ ቅቡልነት ያለው የምናምነው መንግሥትም ሆነ የሕግ ተቋም የለንም። ስለዚህ ”ስጋቱ እውነት ነው” ቢሉን እንኳን ለማመን እንቸገራለን። (እስክንድር ነጋንና ሌሎችንም አሸባሪ ያለ መንግሥት ሌላውን ዜጋ ”አሸባሪ ነው” ሲል ባይታመን ምን ይገርማል? ረስቼው፤ ለካስ እኔም አሸባሪ ነኝ።) ”የአሸባሪነት/አክራሪነት” ክሱ እውነት ሆነም አልሆነ ግን የአወሊያን ጥያቄዎች ሕጋዊነት የሚያስቀር አይደለም። ስለዚህ ለእኔ የአወሊያን ጥያቄዎች መደገፍ ከአሸባሪነት/አክራሪነት እውነታም ሆነ ስጋት ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም።

”የአወሊያ ጥያቄዎች” አገራዊ ፋይዳ

”የአወሊያ ጥያቄዎች” አገራዊ ፋይዳ ከሁለት መሠረታዊ ምንጮች ይቀዳል። አንደኛው የታሪክና የባህል ፋይዳው ነው። ሁለተኛው የዴሞክራሲና የነጻነት አንደምታው ነው። ”የአወሊያ ጥያቄዎችን” የምንደግፍ ዜጎች (ሃይማኖታችን ምንም ይሁን) የምንጋራቸው ሁለት የጋራ መነሻዎችም እነዚሁ ይመስሉኛል።

”የአወሊያ ጥያቄዎች” ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ሌላው ኢትዮጵያዊ በታሪክና በባህል ያላቸውን አብሮ የመኖርና የመቆም ውርስ በድጋሚ የሚፈትኑበት አጋጣሚ ሆኗል። ሙስሊም ላልሆንን ወገኖቼ ታሪክ ያቀበረልን ጥያቄ ቀላል ነው። በእርግጥ ሙስሊም ወንድሞቻችንን እንደ ስጋት ምንጭ እየተመለከትን መጨቆናቸውን በቸልታ እናልፋለን ወይስ የሃይማኖትን አጥር ተሸጋረን ኢትዮጵያዊ ወንዳማማችነታችንን በተግባር እናከብራለን? አለ የምንለውን ስጋት ለማስወገድ የሙስሊሞችን መብት በጭዳነት እናቀርባለን ወይስ መብቱ ከተከበረ ሙስልም ጋራ ስለ ስጋቶቹ የመነጋገር መርህን እንመርጣለን? እንደ አንድ የቤተሰብ አባል ፊት ለፊት ተቀምጠን ስለስጋቶቻችን ለመነጋገርና ለመወቃቀስ የሚያበቃ ብስለት፣ ድፍረት እና ኢትዮጵያዊ እምነት አለን ወይስ የአፈና ምንጭ የሆነው መንግሥት ራሱ ከገዛ ሙስሊም ወንድሞቻችን እና እናቶቻችን፣ ጋብቻዎቻችንና ጎረቤቶቻችን ”ስጋት” እንዲያስጥለን እንፈልጋለን? [ጥያቄው ግን ለሙስሊም ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ጭምር ነው። የክርስቲያን ወገኖቻችሁን ስጋት በመካድና በማቃለል ብቻ ለመመለስ ትሞክራላችሁ ወይስ እንደ አንድ የቤተሰብ አባል ፊት ለፊት ተቀምጣችሁ ስለስጋቶቻችሁና ስጋቶቻቸው ለመነጋገርና ለመወቃቀስ የሚያበቃ ብስለት፣ ድፍረት እና ኢትዮጵያዊ እምነት አላችሁ ወይስ የአፈና ምንጭ የሆነው መንግሥት ከገዛ ክርስቲያን ወንድሞቻችሁ እና እናቶቻችሁ፣ ጋብቻዎቻችሁና ጎረቤቶቻችሁ ”ስጋት” እንዲያስጥላችሁ ትፈልጋላችሁ?] ታሪክ እየተሠራና እየተመዘገበ ነው። በኢትዮጵያዊነት የምነጋራው ታሪክና ባህል በየጊዜው እየታደሰ መሄድ አለበት። አለበለዚያ ተመንዝሮ ያልቃል። የአወሊያ ጥያቄዎች አብሮነታችንን ለማረጋገጥና ለማደስ ካሉን በርካታ አጋጣሚዎች አንዱና ዋናው ሆኖ ይታየኛል። የራስን ቦታ መፈለግ የግል ምርጫ ነው። ውጤቱ የጋራ ነው።

ሁለተኛው የአወሊያ ጥያቄዎች ፋይዳ ከዴሞክራሲና ከነጻነት ፍላጎታችን ጋራ የሚዛመድ ነው። የአወሊያ ጥያቄዎች ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ ባሉ ሕጎች (ሕግ ትርጉም የማይሰጥበት አገር ዜጎች ብንሆንም) አንጻር ሕጋዊ ናቸው። በአንድ በኩል የዜጎችን መሠረታዊ መብቶች መከበር የሚጠይቁ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥትና መጅሊሱ ሕግ እንዲያከብሩ የሚማጸኑ ናቸው። ሲጠቃለል የሕግ የበላይነት እና የሰብአዊ መብት ጥያቄዎች ናቸው። የሕግ የበላይነት የምነለው ሕገ መንግሥቱ በተግባር እንዲከበር ስለሚጠይቁ ነው። የሰብአዊ/ሲቪል መብቶች ጥያቄ የምንላቸው ደግሞ የሃይማኖት ነጻነትን፣ የፈለጉትን አስተምህሮ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመከተል መብት እንዲከበር ስለሚጠይቁ ነው። አሁን በሙስሊሞች ከመነሳታቸው በቀር ጥያቄዎቹ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄዎች ናቸው።

የአወሊያ ጥያቄዎች በአቀራረጻቸውም ሆነ በአቀራረባቸው ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ እሳቤዎችና ግቦች ተቃራኒ እንደሆኑ ካልተረዳን ነገሩ ቀላል ልዩነት ሊመስለን ይችላል። መንግሥት ሁሉንም አይነት ተቋማት እና የሕይወት ገጽታዎች መቆጣጠርና መምራት እንዳለበት ለሚያመነው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ እይታ የሕዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ በቀጥታ መመለስና መጅሊሱን በነጻነት እንዲንቀሳቀስ መልቀቅ መዘዙ ብዙ ነው። ሆኖም የአወሊያ ጥያቄዎችና አቀራረባቸው ለኢሕአዴግ ከምርጫ 97 በኋለ የገጠመው እጅግ ፈታኝ ክስተት ሆኖበታል፤ በሦስት ምክንያቶች።
አንደኛ ጥያቄዎቹ ቀላልና ግልጽ ናቸው። ጥያቄዎቹ በትክክል ከቀረቡ ማንንም ሊያሳምኑ ይችላሉ። ጥያቄዎቹን ለማድበስበስና ”ከአክራሪነት” ጋራ ለማደባለቅ የሚሞከረውም ለዚህ ነው። ሁለተኛ ጥያቄዎቹ የቀረቡት ልል ቡድናዊ ትስስር ባላቸው፣ በከፊል በተደራጁ ዜጎች ነው። እነዚህ ዜጎች የተደራጁ ሲመስሉ የታወቀ ጠንካራ መዋቅር የላቸውም፤ ያልተደራጁ ሲመስሉ ደግሞ ውጤታማ መረጃ የመለዋወጥና የተቀነባበረ እርምጃ የመውሰድ ብቃት አላቸው። ሦስተኛው ምክንያት የተከተሉት ሰላማዊ የትግል ስትራቴጂና ከየትኛውም የተቃውሞ ቡድን ጋራ የተረጋገጠ ትስስር የሌላቸው መሆኑ ወይም ይህ መታመኑ ነው። ይህም መንግሥት እንደወትሮው ቀላል የማሰሪያ ሰበብ እንዳያገኝ አድርጎታል። በደፈናው ኢሕአዴግ ራሱን የሙስሊሞች ነጻ አውጪ አድረጎ የተሰማው የተሳሳተ ግምትም ሳያዘናጋው አልቀረም፤ መጅሊሱን ከሕዝበ ሙስሊሙ ለይቶ መመልከት አልቻለም። የእነዚህ ምክንያቶች ድምር ውጤት መንግሥት መጀመሪያ ደንግጦ እንዲደናበር፣ ቀጥሎ ወዲያውኑ የኀይል እርምጃ እንዳይወስድ አድርገውታል። ይህም ጥያቄ አቅራቢዎቹ የመተዋወቂያና የትግል አጀንዳቸውን የማንጠሪያ ጊዜ እንዲያገኙ አግዟቸዋል። ኢሕአዴግ ከዚህ የሚወስደው ትምህርት ምን እንደሚሆን ተመሳሳይ ንቅናቄዎች ሲነሱ በሚወስደው እርምጃ እንመለከታለን። ከወዲሁ ለማረጋገጥ ግን እንደአሁኑ ጊዜ እንደማይሰጣቸው መናገር ይቻላል።

ወደ አወሊያ ጥያቄዎች ዴሞክራሲያዊ ፋይዳ ስንመለስ አጀንዳዎቹ በመርህም ይሁን በተግባራዊ ውጤታቸው አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሚቃወሙ ናቸው። በአጭሩ ሙስሊሞች መንግሥት የማይቆጣጠረው፣ በእለታዊ ስራው ጣልቃ የማይገባበት ነጻ ተቋም ይኑረን እያሉ ነው። ከዚህ በላይ ፖለቲካዊ ጥያቄ አለ እንዴ! ”መጅሊስ ይውረድ” የሚለው ጥያቄ የቀረበበት መንገድና የተገፋበት በከፊል የተደራጀ ሰላማዊ ስልት አብዮታዊ ዴሞክራሲን በዘላቂነት አደጋው ውስጥ የሚጥል እንደመሆኑ ”መለስ ይውረድ” ከማለት የሚለየው በጥቂት ፊደላት ነው። አራት ኪሎዎች ”መጅሊስ ይውረድ” የሚፈጥረው ተግባራዊ ተሞክሮ ወደ ”መለስ ይውረድ” ሊሸጋገር ይችላል ብለው ቢሰጉ አይፈረድባቸውም።

የአወሊያ ጥያቄዎች መሠረታዊ እሳቤ (አሰምሽን) ዜጎች በነጻነት የመደራጀት መብት እንዳላቸው ታሳቢ ያደርጋል። ዜጎች ተቋሞቻቸውን ከመንግሥት ሕገ ወጥ ተጽእኖና ጣልቃ ገብነት የመከላከል መብት እንዳላቸውም ያምናል። እነዚህ እምነቶች/እሳቤዎች ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋራ ፊት ለፊት የሚላተሙ ናቸው። ለመንግሥት ያለው ምርጫ ጠባብ ነው።

ምርጫ አንድ፤ ጥያቄዎቹን በተለመደውና አሁን በተጀመረው መንገድ ደፍጥጦ መቀጠል። የዚህ ማስፈጸሚያ ሊሆን ይችላል የተባለው የምርጫ ድራማው እየተዘጋጀ ነው ተብሏል። ምርጫ ሁለት፤ ሙስሊሞች ብቻ (መጅሊስ) መንግሥት ጣልቃ የማይገባበት ተቋም እንዲኖራቸው መፍቀድና ጥያቄዎቹን መመለስ። ይህ ማለት በሰፊው የአፈና ባህር መካከል መጅሊሱ ብቻውን የሚኖርበት የነጻነት ደሴት እንደመገንባት ነው። ለጊዜው፣ ግፊቱን ለማለዘብ ካልሆነ በስተቀር ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነው። ምርጫ ሦስት፤ አወሊያን እንደመነሻና መማሪያ ቆጥሮ ጥያቄዎቹን በአዎንታ መመለስ፤ መርሁን ወደ ሌሎች ተቋማትም ማስፋፋት ነው። ይህ ማለት መንግሥት በነጻ መደራጀትን በተግባር ይቀበላል፤ ጥያቄዎቹንም ማስተናገድ ይጀምራል ማለት ነው። ይህ ይሆናል ብሎ ማመን በግሌ ”የሚበር ባለክንፍ ጀበና” ሊኖር ይችላል ብሎ እንደማመን ነው።

የአወሊያ ጥያቄዎች በመርህና በተግባር መመለስ በመሠረቱ ሙስሊም ባልሆኑ ዜጎችም ላይ የሚንጸባረቁ ውጤቶችን ያስከትላሉ፤ አለመመለሳቸውም እንዲሁ። ሁለቱ ጥያቄዎች በመሠረቱ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንንም በቀጥታ የሚመለከቱ ናቸው። አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኙት መሪ (አባ ጳውሎስ ይባላሉ) ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ በመንግሥት ቀጥተኛ ተጽእኖ ”እንደተመረጡ” የታወቀ ነው። የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል የሚባለው ሲኖዶስ በፓትርያርኩ እና በመንግሥት ትብብር ”ለሕዝብ ጥቅም በቁጥጥር ስር መዋሉ” የአደባባይ ምሥጢር ነው። መጅሊስ ብሎ ዶ/ር ሽፈራው ካለ ሲኖዶስ ብሎ ምን ይላል ቢሉ መልሱ አይተ አባይ ጸሐዬ ነው። የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትን አስተዳደር አለመነካካቱን መርጫለሁ፤ በመሠረቱ ግን የተለየ አይደለም።ለማንኛውም ግን የአወሊያ ጥያቄዎች አመላለስ ነገ ለሌሎቹም ሃይማኖቶችና ሲቪክ ተቋማት አርአያ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ነገ እነርሱም መንግሥትን ”ጣልቃ አትግባ” ሊሉ አይደለም?

ጉዳዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ የሞያ ማኅበራትን፣ ሲቪክ ማኅበራትን ሁሉ የሚመለከት ነው። ለዚህም ነው የአወሊያ ጥያቄዎች በመሠረታዊ እሳቤያቸውና ውጤታቸው የሙስሊሞች ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም የዴሞክራሲ ደጋፊ ዜጎች ነው ብዬ የማምነው። ችግሩ ግን ጥያቄዎቹን በዚህ ደረጃ የመተርጎምና የመረዳት ድፍረት መታጡ ይመስለኛል።
ሌላው ነጥብ አንድ ዜጋ የሚያደርገውን ሕጋዊ የመብት ትግል የመደገፍ ሞራላዊና ተግባራዊ አስፈላጊነት ነው። ነጻነትን፣ ፍትሕን ለራሱ የሚፈለግና በዴሞክራሲ የምር የሚያምን ዜጋ ለዚህ መሰል ሕጋዊ ትግሎች ቢያንስ የሞራል ድጋፍ የመስጠት እዳ አለበት ብዬ አምናለሁ።

የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መብት የሚከበረው ከክርስቲያኖች ወይም ከሌላው መብት ላይ ተቦጭቆ አይደለም። ስለዚህ የአንዱ መብት መከበር ሌላውን ሊያሰጋው አይገባም። ይልቁንም አንዱ ነጻ ካልወጣ ሌላው ብቻውን የነጻነት ደሴት ሊሆን ወይም የነጻነት ደሴት ሊገነባለት አይችልም። ሕጋዊ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ የሚገልጹ ወንድሞቻችንንና እኅቶቻችንን ትግል አለመደገፍ አለ የሚባለውን ”አክራሪነት/አሸባሪነት” በተዘዋዋሪ የሚደግፍ እንጂ ስጋቱን የሚቀንስልን አይሆንም። በዴሞክራሲ መርህ አምናለሁ የሚል ዜጋ ሕጋዊ ጥያቄዎቻቸውን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ የሚያቀርቡ ወገኖቹን የመደገፍ የሞራል ግዴታ አለበት። የድጋፉ አይነት ምንም ሊሆን ይችላል። ይህ ሙግቴ የኢህአዴግ ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ ከመሆን ጋራ ቀጥተኛ ትስስር የለውም። ጭፍን ደጋፊውም ሆነ ጭፍን ተቃዋሚው የዚህ ውይይት ተሳታፊም ተጠቃሚም ይሆናል ብዬ አልገምትም። ይህ ከፓርቲ ፖለቲካ በላይ ዋጋ ያለው አጀንዳ መሆኑን አስታውሼ ማለፍ ይበቃኛል።

ዛሬ ሙስሊም ወገኖቹን በኢትዮጵያዊ ወንድማማችነት እና በዴሞክራሲ መርህ ለማመንና ለመደገፍ ድፍረትና ፈቃድ የሌለው ሰው ነገ ተመልሶ ”እንተማመን፤ እንደጋገፍ” ብሎ የመጠየቅ የሞራል መነሻ አይኖረውም። ይህን ድፍረት ማጣት ማለት ለተደገሰልን ያለመተማመን አዙሪት ራስን አሳልፎ መስጠትም ነው። ምርጫው የግል ነው። ውጤቱ የጋራ ነው።

በዚህ ጽሑፍ መጨረሻ ማን ምን ማድረግ ይችላል የሚል ጠቋሚ ሐሳብ እንዲካተት ያስታወሱኝ ወዳጆቼ አሉ። ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። ነገር ግን አንድም ነገር ማብዛት ይሆናል ከሚል፤ አንድም ነገሩ ራሱን የቻለ ሌላ ጽሑፍ ቢሆን ይሻላል በማለት፤ አንድም ሌሎች ሐሳባቸውን ቢሰጡበት እንደሚሻል በማመን፤ በመጨረሻም እየሆነ ያለውን ነገር መረዳት ቅድሚያ ትኩረት ይሰጠው በማለት እዚሁ ላይ ትቼዋለሁ።

በመጨረሻ ይህን ሁሉ ለምን ጻፍኩ? ማርቲን ሉተር ኪንግ በበርሚንግሃም እስር ቤት ታስሮ በጻፈው ዝነኛ ደብዳቤ የሚኖርበትን ከተማ ትቶ በበርሚንግሃሙ ተቃውሞ ለመካፈል የመጣበትን ምክንያት ለወቃሾቹ ሲያብራራ ካለው አንዱ ነገር ትዝ ይለኛል፤ I am in Birmingham because injustice is here. I am at Awelia because injustice is there.

(ስንብት። አክብሮት በኢትዮጵያዊ ፍቅር ለምወዳችሁ ሙስሊም ወንደሞቼና እኅቶቼ! ሌላ የአክብሮት ሰላምታ፣ ለዴሞክራሲና ለነጻነት መርሖች በተቻለ መጠን በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ታማኝ ሆናችሁ ለመኖር ለምትሞክሩ ሁሉ።)

Latest News

video image video image video image Read More

Get Connected

logo link youtube logo link twitter logo link facebook

Contact Information