Ethiopia: የኢትዮጵያ የእስልምና ኃይማኖት ዓሊሞች፣ዲዒዎችና ባለ-ድርሻ አካላት የአንድነትና የትብብር ቃልኪዲን ሰነድ

Group of people having a program

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በኾነው፡፡
የሙስሊሞች አንድነት በኢስላም የላቀ ደረጃ ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ሙስሊሞች አንድ መሆን እንደሚገባቸው አላህ(ሱ.ወ) በተለያዩ የቁርኣን አንቀጾች አበክሮ አዟል፡፡
“ለእናንተ ከሃይማኖት ያንን በእርሱ ኑሕን ያዘዘበትን (ኢስላምን) ደነገገላችሁ፡፡ ያንን ወዳንተ ያወረድነውን ያ በእርሱ ኢብራሂምን ሙሳንና ዒሳንም ያዘዝንበትን ሃይማኖትን በትክክል አቋቁሙ በእርሱም አትለያዩ! ማለት (ደነገግን)” (ሹራ፡ 13)

ሙስሊሞች በአላህ የእምነት ገመድ ሳይለያዩ መያያዝ እንዳለባቸውም ታዘዋል፡፡
“የአላህንም ገመድ ሁላችሁም ያዙ፡፡ አትለያዩም፡፡”(አል ኢምራን 3፡103)
“አላህንና መልክተኛውንም ታዘዙ፡፡ አትጨቃጨቁ፤ ትፈራላችሁ፣ ኃይላችሁም ትኼዳለች፡፡ ታገሱ፤ አላህ ከትዕግስተኞች ጋር ነውና፡፡”(አል-አንፋል፡46)

እኛ ኢትዮጵያውን ሙስሊሞች አንድ እንዳንሆን በተለያየ መልኩ ሊገለጹ የሚችለ ዉጫዊ ተግዳሮቶች ቢኖሩብንም በትዕግስትና በጽናት በጋራ በመቆም ዉስጣዊ አንድነታችንን ለማረጋገጥ ሃይማኖታችን ግዴታ ያደረገብንን ያክል እንደሚጠበቅብን አልሰራንም፡፡ ልዩነቶቻችንን በኢስላማዊ መርህ በትዕግስትና በጥበብ መያዝ ተስኖን መጨቃጨቅ፣ መነታረክ፣ መጣላት፣ የከፉ ቃላትን መለዋወጥና መተማማት በስፋት ተስተዉልብናል።
በዚህ ምክንያት ለሃይማኖታችን፣ለሕዝባችንና ለሀገራችን የቁጥራችንና የሕዝባዊ አቅማችንን የሚመጥን ያክል ሚናችንን ሳንወጣ በርካታ እድልችንን አሳልፈናል፡፡
አንድነታችንን ለማረጋገጥ በተለያዩ ወገኖች የተደረጉት ጥረቶች እንደነበሩ አይካድም፡፡ በተለይም በእነ ሙፍቲ ሀጅ ዑመር እድሪስና ድክተር ጄይላን ከድር ተነሳሽነት በ1999 ተጀምሮ አንድ እርምጃ ከተራመደ በኋላ የተደናቀፈው ጥረት ተጠቃሽ ምሳሌ ነው፡፡የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት እውን የማድረግ ፍላጎቱ በበርካቶች ዘንድ እየተብላላ ቢቆይም በተግባር እውን እንዲሆን የሚፈቅድ አየር ባለመኖሩ ዳግም መንቀሳቀስ አልተቻለም ነበር፡፡ ሆኖም በሕዝበ ሙስሊሙ የዓመታት ዱዓና በመብት ትግል ጉዳዩ ዳግም ወደ አደባባይ ወጥቷል። በተለይም በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን እየተፈጠረ ባለው የለውጥ አየር ዉስጥ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አደራዳሪነትና መልካም ፈቃድ ዘጠኝ አባላት ያሉት የጋራ ኮሚቴም ተሰይሟል፡፡ ኮሚቴዉ
የህዝበ ሙስሊሙን የዉስጣዊ አንድነት እጦት ለማረቅ ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት(መጅሊስ) ያለበትን ዉስንነትና ተያያዥ ችግሮችን እንዲሁም ሌሎች የሕዝበ ሙስሊሙ ችግሮች ላይ የመፍትሄ አቅጣጫ የማመላከትንና የመቀየስን ወቅታዊና ታሪካዊ ኃላፊነትን ተቀብል እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የመፍትሄ አቅጣጫዉም የመጨረሻ ደረጃ ላይ ሲደርስ የህዝበ ሙስሊሙን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ወደ ተግባር ይገባበታል፡፡
እኛ በዚህ ሰነድ መጨረሻ ላይ ስማችንና ፊርማችንን ያስፈርን ዓሊሞች፣ዳኢዎችና የፌደራልና የክልል መጅሊስ ተወካዮች ከከዚህ ቀደሙ ስህተቶች በመማር በመካከላችን ምንም ዓይነት ቀዳዳ ሳንፈጥር ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ ከሚሰራው ዘጠኝ አባላት ካለት ኮሚቴ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት ፣ በትብብርና በአብሮነት ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ግዳታችንን ለመወጣት እንሰራለን፡፡በተለይም፤

1. የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ወይም መጅሊስ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን በሚመጥን፣ ከህዝቡ የተጣለበትን ሀላፊነትን በብቃት መወጣት በሚያስችለው ቁመናና ያለቡድናዊ ወገንተኝነት ኢትዮጵያውን ሙስሊሞችን በሙሉ በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግል ህዝባዊ ተቋም ሆኖ እንዲደራጅ
፤ የሀገራችን የሕግ ማዕቀፎችና አበይት ፖሊሲዎች የያዙትን ትሩፋቶች እስከጥግ ድረስ እንዲጠቀም በሚያስችለው መልኩ እንዲቋቋም የሚጠበቅብንን ሙለ ድጋፍ እንሰጣለን፤

2. ህዝበ ሙስሊሙን ከልዩነትና መናቆር አውጥቶ አንድነቱንና ትብብሩን ማጠናከር ኢስላማዊ ግዳታችን መሆኑን በመረዳት አቅማችን በፈቀደው መጠን ሁለ በኢስላማዊ መርህና የህዝባችንን ፍላጎትና ህልውናውን መጠበቅን መሰረት በማድረግ የየበኩላችንን እንወጣለን፡፡ ለአመለካከት ልዩነትንና ለሀሳብ ነጻነት እውቅና ብንሰጥም የህዝባችን አንድነት የህልዉናችን ጉዳይ በመሆኑ አንድነታችንን የሚጎዳ ዉጫዊና ዉስጣዊ እክሎች እንዳይከሰቱ ለማድረግ በጋራ በመቆም እንታገላለን፡፡

3. የአንድነት እጦት ያደረሰብንን ጉዳትና ያስመለጠንን በርካታ መልካም እድልች በመገንዘብ የአላህን ትዕዛዝ በጋራ ለመወጣት እንድንችል አንድነታችንን በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም ቃል እየገባንና ላለፈውም እርስ በርስ አውፍ በመባባል የጋራ ጥቅማችንን በጋራ ለማስከበር ቁርኣንና ሀዲስን እንዲሁም አራቱን መዝሀቦች መመሪያችን በማድረግ ተግተን በጋራ እንሰራለን፡፡

4. የአንድነት፣የመከባባርና የመተባበር ስሜት ህዝባችን ዉስጥ እንዲሰርጽ ከዛሬ ጀምሮ ታች ድረስ በመውረድ አቅማችን በፈቀደው ሁለ በስፋት እናስተምራለን፤ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በማስቀደም የሚያግባቡንና የጋራችን የሆኑ ጉዳዮችን ማዕከል በማድረግና በመመካከር ከኢስላማዊ አንድነት አልፈን ለሀገራዊ አንድነት ጠንክረን እንሰራለን፡፡ በተቃራኒው ልዩነት ላይ አተኩረው የሚንቀሳቀሱ ወገኖቻችን ካለ በፍቅር፣በኢስላማዊና በወንድማዊ ስሜት ወደ አንድነት ጎዳና እንዲመለሱ እንመክራለን፡፡ በጥበብም
ጥሪ እናደርግላቸዋለን፡፡

5. የህዝባችን አንድነትና ትብብር ለድርድር የማይቅርብ መሆኑን በመረዳት ልዩነቶቻችንን በጥበብና በዘዴ የምናስተናግድበትን ዘላቂ መመሪያ ረቂቅ በኮሚቴው አስተባባሪነት እየተዘጋጀ በመሆኑ ከሁለም ወገኖች በተውጣጡ ዓሊሞችና ምሁራን ከተቃኛ በኋላ በጋራ ገዥ ሰነድነት ለመያዝ ተስማምተናል፡፡ ወደ ፊት የሚቋቋመው የዑለማ ምክር ቤትም ከሁለም ወገን በተውጣጡ የሀገራችን ዑለሞች እንዲደራጅ
ተስማምተናል፡፡ይህንንም በመረዳት ከአሁኑ አብሮ በመስራትና የአመለካከት ልዩነትን በጥበብና በብልሃት በማስተናገድ ለህዝባችን አርኣያ ለመሆን ቃል እንገባለን፤

6. ከላይ ለተጠቀሱት ነጥቦች ተገዢነታችንን ዳግም እያረጋገጥን በጠቅላይ ሚኒስትሩ አደራዳሪነትና መልካም ፈቃድ የህዝበ ሙስሊሙን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የተቋቋመው የጋራ ኮሚቴ ስራውን አጠናቅቆ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጨረሻ መፍትሄ ላይ በፍጥነት እንዲደርስ የሚጠበቅብንን ሁሉ ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡

7. አጠቃላይ ሀገር አቀፍ መፍትሄ እስኪሰጠን ድረስ ከየትኛውም አካል የቱንም ያክል ስሜታችንን የሚኮረኩሩ ክስተቶችና ሁኔታዎች ቢፈጠሩ እንኳ የህዝባችን እና የሀገራችንን ደህንነት በማስቀደም ለሰላማችን የየበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡

8. የኮሚቴው ስራ ተጠናቅቆ የመጨረሻ ምክረ ሀሳብ ይፋ ሲደረግ ኢስላማዊ መርህንና የህዝባችንን ፍላጎት መሰረት ያደረገ እንደሚሆን እየተማመንን እስከዚያው ጊዜ ድረስ በማንኛዉም ምክንያት የሙስሊሞች ተቋማት በተለይም መስጊድች፣የመጅሊስ ቢሮዎችና ሌሎች መሰል ተቋማት የልዩነት፣ የጸብና የግብግብ ስፍራ እንዳይሆኑ የየበኩላችንን ሁሉ ለመወጣት በአላህ ስም ቃል እንገባለን፤ ሕዝባችንም ይህንኑ ስምምነታችንን እንዳተገብር ጥሪ እናደርጋለን፡፡

አላህ ከሀገራችንና ህዝባችን ከክፉውን ሁላ ያርቅልን! አሚን!
ነሐሴ 05 ቀን 2010፤፤አዳስ አባባ፣ ኢትዮጵያ

አላህ ከሀገራችንና ህዝባችን ከክፉውን ሁላ ያርቅልን! አሚን!
ነሐሴ 05 ቀን 2010፤፤አዳስ አባባ፣ ኢትዮጵያ

Click Like -> https://www.facebook.com/ethiopianmuslims

Latest News

video image video image video image Read More

Get Connected

logo link youtube logo link twitter logo link facebook

Contact Information