By Journalism Ishaq EshituImage

ጋዜጠኛ ይሳቅ እሸቱ
የሶማሌ ክልል ጉዳይ አሳሳቢ ነው!

የትኛውም ዓይነት ንጹሃንን ሰለባ የሚያደርግ አካሄድ አገርን የሚጎዳ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚፈጸም ማንነትን መሠረት ያደረገ የጥላቻ ሰበካ እና ጥቃትም እጅጉን የተወገዘ ነው። ከዚህ አንጻር በሶማሌ ክልል በአመራሩ አማካኝነት ሲፈጠሩ የቆዩት ችግሮች እጅጉን ሊያሳስቡን ይገባል።.

የሶማሌ ክልል ለበርካታ አሥርት ዓመታት ከማዕከላዊው ማኅበረ ፖለቲካ ተገልሎ እንዲኖር እና ከመንግሥታዊ ልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን የተደረገ ክልል ነው። በኢሕአዴግ ዘመንም ከፍተኛ ጭቆና እና አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰፍኖበት ቆይቷል። ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገው ደግሞ የኢሕአዴግ አገዛዝ በክልሉ ለሚፈጸመው ሰቆቃ ግዴለሽ መሆኑ፣ ይልቁንም የክልሉን አመራር እንደልቡ ሊቆጣጠራቸው እና በጥቅም ሠንሠለት ሊተሳሰራቸው በሚችላቸው ሰዎች እንዲሞላ ማድረጉ ነው። ከኦብነግ ጋር ሲደረግ በቆየው ፍልሚያ ለረጅም ጊዜ ተጎጂ ሆኖ የቆየውም ከማንም በፊት ምስኪኑ የክልሉ ሕዝብ ነበር።.

ትናንት ከሥልጣን መውረዱ የተነገረው አቶ አብዲ ኢሌ እና አመራሩ ለሶማሌ ወገኖቻችን ደህንነት ቅንጣት የማይጨነቅ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ለረጅም ጊዜ ሲዘግቡት የቆዩት መረጃዎች እና ያወጧቸው መግለጫዎች ይህንን እውነታ ፍንትው አድርገው ያሳያሉ። ራሱ የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ኢሌም በቅርቡ በቴሌቪዥን ቀርቦ ሲፈጸሙ የቆዩት የመብት ጥሰቶች ተጠቃሚ ባደረጉት የደኅንነት አካላት አነሣሽነት የተፈጸሙ መሆናቸውን በመግለጽ ራሱን ከጥፋቱ ነጻ ለማድረግ ሞክሯል። ከዚህ መግለጫው ቢያንስ ክልሉ ነዋሪዎቹን በማሰቃየት ተግባር የተሠማራ መሆኑ ሊካድ የማይችል መሆኑን እንረዳለን።.

ይኸው የአብዲ ኢሌ አመራር ከበርካታ ወራት በፊት ከ800 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ከክልሉ እንዲፈናቀሉ ያደረገ ሲሆን ባለፉት ሦስት ቀናት ደግሞ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን አድርሷል። ከክልሉ የሚመጡት ዘገባዎች የተለያዪ ብሔር አባላት ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን፣ በንግድ ሱቆች ላይም የቃጠሎ ጥቃት መፈጸሙን አሳይተዋል። ቤተ ክርስትያናትም ተቃጥለዋል። ይህ ሁላችንም በጋራ ልናወግዘው የሚገባው እጅግ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ወንጀል ነው። በእምነት ተቋማት ላይ የሚደረግ ጥቃት እጅግ አደገኛ እና በጥብቅ ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው። ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያሉ አካላት ማንኛውንም ተግባር ከመፈጸም የማይመለሱ እና ሃይማኖታዊ/ማኅበረሰባዊ ግጭትን የሚያልሙ መሆኑን የሚያሳብቅ አሳፋሪ ተግባርም ነው። .

የትኛውም ዜጋ በኢትዮጵያ የትኛውም ክልል ማንነቱን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሊደርስበት አይገባም። በብሄሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በፖለቲካዊ አመለካከቱም ሆነ በሌላ መገለጫው ምክንያት የትኛውም ዜጋ በደል ሊደርስበት አይገባም። ይህንን ዓይነት አካሄድ እንደግለሰብ አጥብቄ አወግዛለሁ።.

ከምንም በላይ ይህንን ዓይነት ጥቃት በመፈጸም የክልላቸውን ሕዝብ ለራሳቸው ርካሽ መጠቀሚያነት ማዋል በሚፈልጉ ፖለቲከኞች ወጥመድ ልንወድቅ አይገባም። እነሱ የሚፈልጉት እርስ በእርስ እንድንጠራጠር፣ አንዳችን በአንዳችን እንዳይተማመን እና ሁሉም በየምሽጉ ተደብቆ እንዲታኮስ ነው። ይህንን ዓላማቸውን የምናሰናክለው ደግሞ የበለጠ በመዋደድ፣ ከጅምላ ፍረጃ፣ የጥላቻ ሰበካ እና የዘር ጥቃት በመቆጠብ እንደአንድ ሕዝብ በመሆን ነው። ወንጀለኞቹ መጠቀሚያ የሚያደርጓቸውን ጥቂት ጥቅመኞች አይተን ወንጀላቸውን ወደብሄራቸው እና እምነታቸው ባለመውሰድ ነው።.

አዎን! በሶማሌ ክልል በሶማሌ ሕዝብ እና በሌሎችም ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ ወንጀል ሲፈጽም የቆየው የአቶ አብዲ ኢሌ እና ያደራጀው የወንጀል ቡድን ተግባር በምንም መልኩ ለዘመናት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሲጠብቅ የኖረውን ደጉን የሶማሌ ሕዝብ አይወክልም! ይህንን ሁላችንም መረዳት ይኖርብናል።.

ወንጀለኞች ሁልጊዜም ከሕዝብ ጀርባ መደበቅ ይፈልጋሉ። የሚሠሩት ወንጀል የእነሱ ሳይሆን የመጡበት ብሄር፣ ሃይማኖት ወዘተ እንደሆነ ሊሰብኩን ይፈልጋሉ። ከእነሱ ጋር ሳይሆን ከወጡበት ሕዝብ ጋር እንድንጋጭ ይፈልጋሉ። ይህንን እኩይ አካሄድ የምንከላከለው ታዲያ እንድናደርገው የሚፈልጉትን ባለማድረግ ነው። በወጥመዳቸው ከመውደቅ በመጠንቀቅ ነው። ከዚህ አንጻር ሁላችንም ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል ብዬ አምናለሁ።.

የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ መንግሥት አካባቢውን በማረጋጋት እና የደረሰውን ጉዳት በመጠገን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም አደራ እላለሁ። ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን፣ ለወደሙ ተቋማት መልሶ መቋቋምን፣ ለፈረሱ የእምነት ተቋማትም ፈጣን መልሶ ግንባታን እመኛለሁ! አላህ ኢትዮጵያችንን ከአደጋ ይጠብቅልን! ሊያበጣብጡን የሚሹትን በሩቁ ይያዝልን! የማይበጁንን ሤረኞች ከዙሪያችን ያርቅልን! አሚን!

Latest News

video image video image video image Read More

Get Connected

logo link youtube logo link twitter logo link facebook

Contact Information